ሰማያዊው ቤተ መቅደስ

ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው መልዕክቱ ላይ እንዲህ አለ« ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠው እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን  እርሱ/ክርስቶስ/ የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው እርሷም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት»ዕብ 8፥1 የእግዚአብሔርን ከሃሊነትና መለኮታዊ ጥበብ ደካማው የሰው አእምሮ መርምሮ ሊደርስበት ከቶ የማይችል ነው በሰማያት ምን ዓይነት ቤተ መቅደስ አለ? ከምን ዓይነት ቁስ ተሰራ?ቅርጽና ይዘቱስ ምን ይመስላል?ወርድና ስፋቱንስ ማን ሊያውቀው ይችላል? ይህ ሁሉ ጥያቄ ከመሆን በቀር ሥጋና ደም መርምሮ የማይደርስበት ጥልቅ ሐሳብ ነው ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክ ለወዳጆቹ ያዘጋጀው ስፍራ ከሰው የአእምሮ ጥልቀትና የልብ ስፋት የረቀቀ ነው ፤ነገር ግን ስለዚህ ቤተ መቅደስ የምንናገረው ዋና ነገር ቢኖር በውስጧ የሚያገለግለው ሊቀ ካህን ክርስቶስ ኢየሱስ  መሆኑንና መቅደሱም አማናዊ የዘላለም የማምለኪያ አፀድ መሆኑን ነው ።

ዕፁብ ድንቅ! እውነተኛ ሊቀ ካህን ያለበት ቤተ መቅደስ የእረፍት መፍሰሻ ነው በውስጧ ያለው ሰላምም ዳርቻ የለውም አምልኮው የእውነትና የመንፈስ ስለሆነ ለነፍስ ቅድስናንና ሐሴትን ከማብዛቱም በላይ የመለኮት ባህርይ ተካፋይ የሚያደርግ ነው። በጸጋ ብርሃን በተሞላው ፣በክብር ደመና በተጋረደው ፣ከሰንፔርና ከዕንቁ ይልቅ በሚያብረቀርቀው የብርሃን ዓምድ ሥር ቆሞ የልጁንና የአባቱን ዙፋን መባረክ እንዴት ደስ ይላል ጣራና ግርግዳው መቃንና ጉበኑ የቃላት ጉልበት ሊገልጸው በማይችል የብርሃን ደመና ክበብ ውስጥ በቀስተ ደመና መንጦላዕት ተጋርዶ ድካምና መስልቸት በሌለበት የቅድስና ሥፍራ የብርሃን ዘውድ ደፍቶና የዘንባባ ዝንጣፊ ጨብጦ ከበረድ ይልቅ የነጻ የክብር መጎናጸፊያ ደርቦ ከአእላፍት መላእክት ጋር ቅዱስ ፣ቅዱስ፣ቅዱስ እያሉ ለምስጋና መሰለፍ ምን ዓይነት መመረጥ ይሆን!?

ሰማያዊው  መቅደስ!! ምሥጋና ብቻ፣አምልኮ ብቻ፣ ዝማሬ ብቻ የመላበት ንጹህና ቅዱስ ስፍራ፤ አንዱ ሌላውን የማያይበት የሚታይ አንድ ብቻ የሆነበት አንዱ ስለሌላው የመያስብበት የሚታሰበው  አንዱ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ብቻ የሆነበት መሪና ተመሪ አዛዥና ታዛዥ ባሪያና ሎሌ ከሳሽና ተከሳሽ የሌለበት ሁሉ አንድ ሁሉ በአንድ ሁሉ ለአንድ የሚቆምበት የጽድቅ መካን።

ሰማያዊው መቅደስ!! ሸፍጥና ተንኮል የማይታወቅበት በአለባበስና በአነጋገር መንፈሳዊ መስሎ አድማና ሴራ የመይሸረብበት መንፈሳዊ ቃላት ምላስ ላይ እየደረደሩ የጥፋት ጉድጓድ በጎን የማይምሱበት ዘረኝነትና ጎጠኝነት ስማቸው የማይታወቅበት የሐሰት መሀላና ክስ ደብዛቸው የጠፋበት ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ልብሰ ተክህኖና ፈረጅያ ተለብሶ ለፍቅረ ንዋይናለሥልጣን የማይራኮቱበት የጽድቅ አደባባይ።

ሰማያዊው መቅደስ!! ለዝና የማያገለግሉበት እኔ ብቻ ልታይ የማይባልበት በመንፈሳዊ ካባ ሽፋን ለሥጋ ክብር የማይዋደቁበት አንድ የበቃና የታመነ ደግሞም የሚራራ ታምኝ ሊቀካህን ኢየሱስ ብቻ ያለበት እርሱን ብቻ እየሰሙ እሱን ብቻ እያዩ በእርሱ ብቻ እየተገለገሉ የሚኖሩበት እፁብ ድንቅ የተድላ መፍሰሻ ምን ዓይነት ድንቅ ሥፍራ ነው!ምንስ ዓይነት የእረፍትና የእርካታ ሥፍራ ነው እንክሮና ተደሞ ለዚህ ስፍራ ይገባል።

ወዳጄ የክርስትናችን መጠቅለያ ይህ ስፍራ ነው   እምነታችን ሰማያዊ ጉዟችን ለሰማያዊ ዓላማችን ደግሞ ውዳችን ጋ መድረስ ነው የእምነታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህን ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳለበት የእረፍት ቦታ ደርሶ በዘላለም የእረፍት ፈሳሽ ዳርቻ እርካታው ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔርን ቅድስናና ክብር መካፈል ነው።

ጠላት ዲያብሎስ የክርስትና ጎዳናችንን ዳርቻ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ወደዛ ክብር እንዳንደርስ ስንቱን አደረገን?ስንቱን አስረገጠን ስንቱንስ አስመኘን? በምድራዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ የምንገኝ አገልጋይና ምእመናንን ሰማያዊው ቤተ መቅደስን እንዳንመለከት ስንቴ ጋረደን በምድር የጀመርነውን አምልኮ በሰማያዊቷም ስፍራችን እንዳንቀጥል ከጸጋው ዙፋን ሥር ሊያርቀን ምን ያላደረገን አለ? አንዳንዶቻችንን ለሥልጣንና ለታይታ ሲያባላን አንዳንዶቻችንን ደግሞ በፍቅረ ንዋይ ናላችንን አዙሮ የሰማዩን ብልጥግና ሳይሆን እንደ እንፋሎት ታይቶ የሚጠፋውን የዚህ ዓለም ክብር እያስመኘ ከወገኖቻችን ጋር ሲያናክሰን ጥቂት የማንባለውን ደግሞ በመቅደሱ ሊታይ የሚገባውን ጌታ ከማሳየት ይልቅ ራሳችንን እንድናሳይ ለከንቱ ዝናና ክብር በመዳከር በቅዥት ዓለም ውስጥ ሲያንገላውደን አንዳንዶቻችንን በመቅደስ ለማምለክ ሳይሆን ለመመልክ እንቅልፍ ሲነሳን ኖሯል።

አንተ የተኛህ ንቃ!! አንቸም ንቂ! ክርስትናችን የሰማያዊ ሃገር ጉዞ ጅምር ነው መጨረሻው ላይ ሳይሆን ገና መግቢያው ላይ ነው ያለነው ዓይንህን አንሳና ሰማያዊውን ቤተ መቅደስ ተመልከት እዛነው ዳርቻህ አዛነው ማረፊያሽ ዋናው ቤታችን የሚራራው ሊቀ ካህናችንም በዚያነው መገኘው ። ለሰበካ ጉባዔ ሥልጣን ፣ለኮሚቴ አመራርነት እየተባላህ ዓይንህን አትጋርደው ሁሉም ተራ ነው ዓይንህን ግለጥ በሰው እጅ የተተከለውን የምድር ቤተ መቅደስ ጣራና ግድግዳ እያደንቅህ እኔ ገዛውት እኔ ሰራውት እኔ አደስኩት እኔ ብቻ ልኑርበት እኔ ብቻ ልታይበት እያልክ ፍቅር አጥተህ ከወገንህ ጋራ ስትባላ አትኑር አንተም ቤተ መቅደሱም ፈራሾች ናችሁ ሁለታቹም በምድር ቀሪዎች ናቹ ወዳጄ! ይልቁን እግዚአብሔር በእጁ የተከላትን ሰማያዊ ቤተመቅደስ እየተመለከትክ በፍቅርና በይቅር ባይ ልብ ተስማምተህ ኑር የምድሩን ስትመኝ የሰማዩን እንዳታጣ  ሕያው ሥልጣን የለም ዘላለማዊ ዝናም የለም ሁሉ እንደጠዋት ጤዛ ታይቶ የሚጠፋ እንደ ምድረ በዳ አበባም እረጋፊ ነው ፤ የሆነቦታ ላይ ተሰብስበህ ለመሰረትከው ማህበር ሳይሆን ለጌታ ክብር መኖር ጀምር ጥቂቶችን ለማስደሰት ብልህ በአእላፍቱ ዘንድ ጥላቻን አታትርፍ ለሥጋውያን ሹማምንቱ ደስታ እየታገልክ የሞተልህን ጌታ ደግመህ አትስቀለው ሆድህን ሞልተህ ህሊናህን ጦም አታሳድረው የሚገርምህ ዛሬ እንተ የምትነካካሰብትንና ከወንድምህ ጋራ በጥላቻ የምትካሰስበትን ጉዳይ ትናንት ሌሎች እንዳንተው አድርገውት ነበር ግን ሁሉም ጥለውት በሞት ተጠቅልለዋል ምናልባት አንተ ባለህበት ሰፈርና ሃገር  አላየህ ይሆናል ታሪክ ብትመረምርና ብትጠይቅ ግን አንድ ሺ አንድ ቦታ ታገኛለህ የሚያሳዝነው ዜና ግን ይህን ሁሉ ያደረገው ወደ ምድር የተጣለው በዓለመ መላእክት ጸብና ጭቅጭቅ የጀመረው የጥፋት ልጅ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። በክርስቶስ ስም የታሰረ ይሁን። ይህ ክፉ ጠላት ነው እንግዴ አማናዊቷን ድንኳን ሰማያዊቷን መቅደስ በተመስጦ አንዳናይ ውሳጣዊ ዓይናችንን  ጋርዶ ከሊቀ ካህናችን ከኢየሱስ ጋር በፍቅር እንዳንጣበቅ እያዘናጋን ያለውና በብርቱ ጸሎት እንዋጋው ዘንድ ግድ ይላል ሰማያዊውን መቅደስ ዓይነ ልቦናችንን ከፍተን በማስተዋል አናይ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ያግዘን አሜን።

ከመ/ር ታሪኩ አበራ

www.tarikuabera.org

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *